ግልጽ ደብዳቤ ለፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

ግልጽ ደብዳቤ ለፕ/ር ብርሃኑ ነጋ
በኢፌዲሪ የትምህርት ሚኒስቴር፣ ሚኒስትር
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

ጉዳዩ፣ 12ኛ ክፍል ፈተና ስለታገዱት 12,787 ተማሪዎች ይቅርታ እና ተገቢ ቅጣት ስለመጠየቅ

ኢትዮጵያን ለዜጎቿ የተመቸች ለማድረግ፣ ዘመናዊ እና ቀልጣፍ የአሰራር ሂደቶችን የሚረዳ እና በስራ ላይ የሚያውል፣ የዜጎችን ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በጥልቀት እና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ማጥናት የሚችል እና ተግባራዊ መፍትሄዎችን የሚጠቁም፣ በየዓመቱ ለሚጨምረው የሕዝብ ቁጥር ተመጣጣኝ የእርሻ እና ኢንዱስትር ምርቶችን ማምረት የሚያስችል ተጨባጭ ዕውቀት ያለው፣ አገራዊ እና ዓለማቀፋዊ ፖለቲካዊ ሁነቶችን በአግባቡ የሚረዳ እና የሚተነትን፣ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ደህንነት ፋይዳ እና ኢትዮጵያ ልትጫወት የምትችላቸውን ዓለማቀፋዊ ሚና በአገባቡ የሚረዳ፣ በእውቀት የታነፀ ማሕበረሰብ መገንባት ወሳኝ ነው።

ትውልድን በመቅረጽ እና የኢትዮጵያን እድገት በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ ትምህርት ሚኒስቴር ዋነኛው ሞተር እንደሆነ ቢታወቅም፣ ለበርካታ ዓምታት ለውጥ ማምጣት አልቻልም ነበር። በዚህ ረገድ፣ እርስዎ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን መምራት ከጀመሩ በኋላ ሚኒስቴር መ/ቤትዎ የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ ለሚያስችሉ ስራዎች ቅድሚያ ትኩረት በመስጠት ያቀዳቸው እና እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት እጅግ ተስፋ ሰጪዎች ናቸው። እገራችን ኢትዮጵያ እንድታድግ፣ እነዚህን ተስፋ ሰጪ ተግባራት በማጠናከር፣ የሚገጥሙ ተግዳሮቶችን በእውቀት አርሞ ማለፍ  እና የማሻሻያ ሃሳቦችን በአግባቡ መከወን ያስፈልጋል።

ክቡር ሚኒስትር፣ ይሄንን ጽሑፍ ለክቡርነትዎ በቀጥታ ለመጻፍ ያነሳሳኝ የሚከተለው ጉዳይ ነው። ይኸውም፤ ከመስከረም 30 እስከ ጥቅምት 2፣ 2015 ዓ/ም በተሰጠው የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂ ፈተና ወቅት “በገዛ ፈቃዳቸው ፈተና አቋረጡ” የተባሉት 12,787 ተማሪዎች “ለሌሎች መማሪያ እንዲሆኑበሚል ሰበብ ሙሉ ለሙሉ ከፈተና የመታገዳቸው ነው። የእነዚህ ተማሪዎች ጉዳይ ስለአገሩ እንደሚቆረቆር እና የአቅሙን አስተዋጽዖ እንደሚያደርግ አንድ ዜጋ እረፍት ስለነሳኝ እና በበርካታ አጀንዳዎች በተወጠረችው አገራችን የተማሪዎቹ ቁጥርነት እንጂ አምራች ዜግነት ጨርሶ እንደተረሳ ስለተሰማኝ ነው።

ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ተፈታኝ ተማሪዎች እና የፈተና አስተናባሪዎች በተሳተፉበት የፈተና ሂደት፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ያሉትን ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ነባራዊ ሁኔታዎች ማገናዘብ ተገቢ ነው። ከሂደቱም፣ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን እንደትምህርት በመውሰድ ለሚቀጥለው እንደ ግብዓት መጠቀም ሲቻል፣ ግዴለሽነት እና እልህ የተጫነው በሚመስል መልኩ ከ12,000 በላይ ተማሪዎችን ያለበቂ ምርመራ በአንድ ቀን ስሕተት የ12 ዓመታት ልፋታቸውን ውጤት እንዳያዩ ድጋሚ እንዳይፈተኑ ውሳኔ ማሳለፍ ስሕተት ነው ብዬ ስለማምን ነው። ሂደቱም በተገቢው መንገድ ካልታረመ የታሰበው የትምህርት ጥራት የማረጋገጥ ሥራን ገና ከመጀመሩ፣ የማያስፈልግ፣ የማይገባ እና የማይረሳ ጥቁር ጠባሳ አሳድሮ ያልፋል። የውሳኔውን ፖለቲካዊ አሉታዊ ጎኖች በመተው፣ ማሕበራዊ እና አገራዊ ችግሮቹን በጥቂቱ ልጠቁም።  

የእገዳው ማሕበራዊ እና አገራዊ ችግሮች

ክቡር ሚኒስትር፣ ምንም እንኳን ጉዳዩ ብዙ ሙያዊ ትንተና የማያስፈልገው እና በወቅቱ “መፍትሄ የተሰጠው” ቢመስልም፣ የተሰጠው “መፍትሄ” ከመፍትሄነቱ ይልቅ እንደ አገር ብዙ ችግሮችን የሚፈጥር እንደሆነ፣ የዜጎቻችንን ማህበራዊ እና ስነልቦነዊ አሁናዊ ሁኔታዎች ግርድፍ ዳሰሳ በማድረግ መተንበይ ይቻላል። እናም ጉዳዩን በየደረጃው በሆደ ሰፊነት ዳግም ማጤን እና ፍትሃዊ የሆነ እና የተሻለ አስተማሪ መፍትሄ መስጠት በጊዜ ብዛት አፍጥጠው የሚመጡ ችግሮችን ከወዲሁ ማስቀረት፣ ትውልድን ማነጽ እና አገርን መገንባት ያስችላል እና በእጄ ይበሉኝ።

  1. አገራዊ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት፤ አንድ ተማሪ በወር በአማካይ አንድ ሺህ ብር የሚያስወጣ ቢሆን፣ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ት/ቤቶችን ወጪዎች ትተን አንድ ተማሪ 12ኛ ክፍል ለማጠናቀቅ (1,000 X 10 ወራት X 12 ክፍሎች) = 120,000 (አንድ መቶ ሃያ ሺህ) ብር ያስወጣል። ይሄም በጠቅላላዎቹ 12,787 ተማሪዎች ሲሰላ፣ (12,000 X 12,787) = 1,534,440,000 (ከአንድ ቢሊየን አምስት መቶ ሚሊየን በላይ ) ብር ይሆናል። እናም በአንድ ጀምበር በተከሰተ ስህተት ይሄንን የሚያክል የቤተሰብ እና የአገር ሃብት ያለተገቢ የፈተና መቋጫ መደመደም የለበትም የሚል እምነት አለኝ እና በድጋሚ ቢጤን። የዚህ ነጥብ ቁምነገር፣ የአንድን ተማሪ የማስተማሪያ ወርሃዊ ወጪ ከፍ ወይም ዝቅ በማድረግ የሚያስማማ ስሌት ላይ መድረስ ሳይሆን፣ ተማሪዎቹን እስከመጨረሻው የማገድ ኢኮኖሚያዊ ጉዳቱን ማሳየት እና ውሳኔው ዳግም እንዲጤን ለመጠየቅ ነው።
  2. የቤተሰብን ስነልቦናዊ ስብራት፤ አንድ ተማሪ የሚኖርበት ቤተሰብ በአማካይ 5 አባላት (ተማሪው፣ እናት፣ አባት፣ እና ሁለት ወንድም/እህት) ቢኖሩት፣ (5X12787) = 64,000 የሚሆኑ የቤተሰብ አባላት የውሳኔው ቀጥተኛ ተጎጂዎች ይሆናሉ ማለት ነው። በተለይ መጤን ያለበት፣ ውሳኔው የተወሰነባቸው ተማሪዎች መኖሪያ አካባቢዎች በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በተከሰተው ጦርነት ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆኑ ችግሮች ገፈት ቀማሽ መሆናቸውን ነው። ከዚህም አንፃር፣ እነዚህ ቤተሰቦች በርካታ ውጣውረዶችን ካሳለፉበት ጦርነት ገና በአግባቡ ሳያገግሙ እና ግራ ቀኙን ለማመን በሚቸገሩበት ወቅት ተስፋ የሰነቁባቸው ልጆቻቸው እንዲህ ያለ “መዓት” ሲያመጡባቸው የሚሰማቸውን ስሜት ማጤን ሰብዓዊነት ነው። አግባብ ያለው ውሳኔ መወሰን የተማሪዎቹን ብቻ ሳይሆን ከስልሳ ሺህ በላይ የሚሆኑ ቀጥተኛ ተጎጂ የቤተሰብ አባላትን ስነልቦናዊ ስብራት መጠገን ያስችላል።
  3. ስደተኝነትን እና ተያያዥ ችግሮች፤ አትፈተኑም ከተባሉ ተማሪዎች መካከል ጥቂት የማይባሉት በአገራቸው ተምረው እና ሰርተው የመለወጥ ተስፋ ስለሚያጡ እና ባደጉበት ማሕበረሰብ የጥፋተኝነት እና የመገለል ስነልቦናዊ ጫና ሊደርስባቸው ስለሚችል፣ ወደ ተለያዩ አገራት በሕገወጥ መንገድ የመሰደድ እጣቸው ከፍተኛ ይሆናል። ይሄም በተለያዩ አገራት ተሰደው ያሉ ወገኖቻችን ላይ እየደረሰባቸው ያለውን ሞት እና ሰቆቃ ለመቀነስ በመንግስት እና በተለያዩ በጎ አድራጎት ድርጅቶች እየተሰራ ያለውን ሥራ ማቆሚያ እንዲያጣ ያደርገዋል። ስለዚህ አሁን በስደት እየሞቱ እና እየተሰቃዩ ያሉ ወገኖቻችን ግድ እንደሚልዎ ስለማምን እና ሊሰደዱ ከሚያስቡ 100 ተማሪዎች እንኳን ከዚህ መንገድ ማስቀረት የሕይወት ማዳን ውሳኔ መሆኑን ክቡርነትዎ እንደሚረዱ አምናለሁ።

ውሳኔው በድጋሚ ቢጤን አማራጭ መፍትሄዎች

ክቡር ሚኒስትር፣ ከካበተ የትምህርት እና የሕይወት ልምድዎ እንደሚያውቁት፣ ትምህርት በቀጥተኛ ብቻ ሳይሆን በተዘዋዋሪ መንገድም የሚገበይ ሃብት ነው።  ተማሪዎችንም ከቀጥታው የክፍል ውስጥ ትምህርት በተጨማሪ ይቅርታን እና ፍትሃዊነትን ማስተማር የሚቻልበት አጋጣሚ ስለሆነ፣ ውሳኔውን በድጋሚ እንዲጤን ደንደሚያደርጉ ተስፋ አደርጋለሁ። ውሳው በድጋሚ እንዲጤን ስጠይቅ፣ ተለዋጭ መፍትሄም መጠቆም ተገቢ መሆኑን እረዳለሁ። በመሆኑም፣ ከተማሪዎቹ አድማ ጋር ተያይዞ በፈተና ማዕከላቱ ለተከሰቱ ችግሮች ተጠያቂነት እንዲኖር እና አድማውን በመሩ እና በተሳተፉ ተማሪዎች ላይ እንደየተሳትፏቸው አስትማሪ ቅጣቶች መስጠት እንዲያስችሉ የሚከተሉትን አማራጭ ሃሳቦችን እጠቁማለሁ።

  1. ዋነኛ አሳዳሚዎች ተለይተው በሕግ እንዲቀጡ ማድረግ፤ የ”አንፈተንም” አድማውን በዋነኝነት የመሩ እና ያስተባበሩ ተማሪዎችን (ከተመሳሳይ ቅጽበታዊ አድማዎች አንፃር ጠቅላላ አሳዳሚዎቹ ከ10 እስከ 15 ላይበልጡ ይችላሉ) በተለያየ የማጣሪያ መንገድ መለየት እና አድማዎቹን በመፈተኛ ማዕከላቱ ከተገኙበት ዋነኛ ዓላማ ውጭ የሆነ አጀንዳ ለማስፈጸም መሆኑ በምስክሮች ከተረጋገጠ፤ ተመጣጣኝ አስተማሪ እና ሕጋዊ ቅጣት እንዲተላለፍባቸው ማድረግ።
  2. የአድማው ተከታይ ተማሪዎችን ማሕበራዊ አገልግሎት ማሰራት፤ ተመሳሳይ አድማ እንዳይሳተፉ እና ትምህርት እንዲያገኙ፣ በአድማው ዋነኛ ሚና የሌላቸው ተማሪዎች እንደየአካባቢው ነባራዊ ሁኔታ ማሕበራዊ አገልግሎት እንዲሰጡ (ለምሳሌ ምርት ስብሰባ፣ አካባቢ ማጽዳት፣ ችግኝ መትከል፣ አረጋዊያንን በሥራ ማገዝ፣ ወዘተ) ማድረግ እና ካሉበት ከተማ፣ ቀበሌ እና ገበሬ ማሕበር የአገልግሎት ማረጋገጫ ማስረጃ እንዲያቀርቡ ማድረግ።
  3. የፈተና ወጪያቸውን በከፊል እንዲሸፍኑ ማድረግ፤ የ2016ዓ/ም ፈተና ማዕከላት እንደ 2015ቱ ዩኒቨርሲቲዎች ከሆኑ፣ የተቀጡት ተማሪዎች የራሳቸውን መጓጓዣ እና ሌሎች ተያያዥ ወጪዎችን (ለምሳሌ ምግብ) ተተምነው ከመንግስት ጋር በመጋራት በከፊል እንዲሸፍኑ ማድረግ ሊያስተምራቸው የሚችል አማራጭ ይሆናል።

ማጠቃለያ

ክቡር ሚኒስትር፣ በሚኒስቴር መስሪያ ቤትዎ፣ የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት በጥልቀት የታቀዱ እና የአተገባበር ሂደቶች በዝርዝር እንደተቀመጠላቸው ባምንም፣ ሙሉ ለሙሉ በሥራ ላይ ለማዋል፤ የወላጆች፣ በየደረጃው ያሉ ተማሪዎች እና መምህራን፣ እንዲሁም ሌሎችን የትምህርት መስኩ ባለድርሻ አካላትን ግብዓት፣ ተሳትፎ እና እገዛ እንደሚያስፈልገው እረዳለሁ። በዚህ ረገድም፣ እኔም በሙያዬ እና በምችለው የበኩሌን ለማድረግ ቃል እገባለሁ። ከዚሁ ጋር አያይዤም፣ የነገዋን ኢትዮጵያ ከሚረከቡት መሃል ስለሆኑት 12,787 ተማሪዎች ያቀረብኩትን ሃሳብ በቅንነት፣ ለትውልድ እና ለአገር በመቆርቆር መሆኑን እንዲረዱልኝ እጠይቃለሁ።  ጥያቄዬን እና ሃሳቤን በመገምገምም የሚኒስቴር መ/ቤትዎ ገንቢ እና አስተማሪ ውሳኔዎችን እና ዝርዝር የአፈፃፀም መመሪያዎችን በጥልቀት ተወያይቶ ለተማሪዎቹ እና ለሚመለከታቸው አስፈፃሚ አካላት እንደሚያሳውቅ ሙሉ እምነት አለኝ። ለተማሪዎቹ አፋጣኝ መፍትሄ እንደሚሰጡ በማመን አክብሮቴን እና ምስጋናዬን አበክሬ አቀርባለሁ።

ደነቀው አበራ ጀምበሬ (ፒኤችዲ)

Written by 

2 Replies to “ግልጽ ደብዳቤ ለፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ”

  1. That s why it is recommended to be careful when taking an aromataseinhibitor during testosterone replacement therapy as this drug might mess with the normal levels of aromatase and lead to brain complications where to buy cialis online safely Yet at the end of it, if you d got those Oistrakh and Richter concerts or you d got the Bolshoi you d think it was worth it

Comments are closed.