ይድረስ ለሚመለከተው (ለትምህርት ሚኒስቴር)

በደነቀው አበራ ጀምበሬ

ኢትዮጵያ ውስጥ ከኮሮና ወረርሺኝ ክስተት ጀምሮ፣ በየደረጃው ያሉ ትምህርት ቤቶች እንዲቆሙ እና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርት ይከታተሉ የነበሩ ተማሪዎች ወደየቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ ተደርጓል። ትምህርት ሚኒስቴር ባወጣው መመሪያ መሰረትም፣ ከማስተርስ እና ፒኤችዲ ተማሪዎች በስትቀር የመጀመሪያ ድግሪ ተመራቂ ተማሪዎች በዚህ ዓመት እንደማይመረቁ ተገልጿል። ሰሞኑን የሚለቀቁት መረጃዎች እንደሚያሳዩትም፣ በወረርሺኙ እየተጠቁ ያሉ ወገኖቻችን ቁጥር ከቀን ወደቀን በማሻቀብ ላይ ይገኛል። ወረርሺኙ ሊቀንስ ወይም ሊጠፋ ይችላል በሚል እሳቤ፣ ትምህርት ቤቶች እና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በሚቀጥለው (2013 ዓ/ም) የትምህርት ዘመን እንደቀድሞው ሙሉ አገልግሎት እንዲሰጡ ማስብ እና መዘጋጀት ተገቢ ቢሆንም፣ ወረርሺኙ ከቁጥጥር በላይ ቢሆን በሚል ተለዋጭ መፍትሄዎችን ማሰብ እና በትይዩ መዘጋጀት ተገቢ እንደሆነ አምናለሁ። ስለሆነም በየደረጃው ያሉ የሚመለከታቸው የፌደራል እና የክልል መንግስት ተቋማት፣ ወረርሺኙን በትጋት ከመከላከል በተጨማሪ፣ በሚቀጡሉት ሁለት እና ሶስት ወራት፣ የ2013 ዓ/ም ዓመት ትምህርት ሂደትን እንዴት ማከናወን እንደሚኖርባቸው ማሰብ እና መዘጋጀት ይኖርባቸዋል። ለዚህም እንዲጠቅም፣ የየዘርፉ ባለሞያዎች በተሻለ መልኩ እንደሚያስቡባቸው እና የተሻለ መፍትሄ እንደሚያዘጋጁ እምነት ቢኖረኝም፣ በበኩሌ አንዳንድ የመፍትሄ ሃሳቦች ልጠቁም።

1. ማስተማሪያ መንገዶችን በሚመለከት

ሀ. ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ቴሌኮምዩኒኬሽን

  • ከፍተኛ የትምሕርት ተቋማት፣ ተማሪዎች በርቀት ትምህርት እንዲከታተሉ የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ መተግበሪያዎችን (online systems) ለምሳሌ (Zoom, Blackboard Collaborate ወይም Microsoft Teams) መከራየት (subscribe ማድረግ)፣
  • ቴሌኮምዩኒኬሽን፣ ተማሪዎች በስልክ ወይም በኮምፒውተር ትምህርት በርቀት በዝቅተኛ ዋጋ እንዲከታተሉ ለማገዝ የተማሪዎችን ወርሃዊ የኢንተርኔት አገልግሎት ከፍያ ከፍተኛ ቅናሽ በማድረግ፣ የተማሪ ኢንተርኔት ፓኬጅ ማዘጋጀት እና ለአፈፃጸሙ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር የሚሰራ ቲም ቢያዋቅር።

ለ.  ለሁለተኛ ደረጃ እና ከዚያ በታች ላሉ ት/ቤቶች

  • የአስራአንደኛ እና አስራሁለተኛ ክፍል ተማሪዎችን (ስልክ ስለሚኖራቸው) በተለየ ትኩረት እና ክትትል የሚደረጉበትን መፍትሄ ማሰብ። የመምህራን ፈጠራ የታከለበት፣ ቢያንስ በሳምንት አንድ ጊዜ ከየትምህርት አይነቱ መምህር፣ የክለሳ የስልክ ኮንፈረንስ እንዲከታተሉ ማድረግ።
  • አስረኛ እና ከዚያ በታች ላሉ ተማሪዎች የየአካባቢውን የኑሮ ሁኔታ እና ቋንቋ ያገናዘበ የርቀት ትምህርት ስርጭት ማድረግ፣
  • ለምሳሌ፤
    • ከሰባተኛ እስከ አስረኛ ላሉ ተማሪዎች፣ የክልል የቴሌቭዥን ጣቢያዎች ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በየትምህርት አይነቱ እና በየክፍል ደረጃው የሚታወቁ መምህራንን ተከታታይ ዝግጅት እንዲያቀርቡ መርሃግብር ማዘጋጀት።
    • ለመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች ትምህርት በሬዲዮ በተጠናከረ መልክ ለማሰራጨት ዝግጅት ማድረግ እና አስፈላጊ ግባቶችን ማመቻቸት። 

2. የማስተማሪያ መርጃዎችን ዝግጅት በሚመለከት

ሀ. ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት

  • ዝርዝር እቅድ (course outline)፣ በየትምህርት አይነቱ መምህራን የማስተማሪያ እንዲያዘጋጁ ማድረግ
  • የማስተማሪያ ስላይዶች፣ እንደየአስፈላጊነቱ እና የትምህርት አይነቱ የየትምህርት ዓይነቱ መምህራን እንዲያዘጋጁ ማድረግ
  • የመምህራን ስልጠና፣ በርቀት ለማስተማር የተመረጡ የቴክኖሎጂ ግባቶችን በአግባቡ መጠቀም እንዲችሉ ለመምህራን እና የሚመለከታቸው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (IT) ባልሞያዎች ስልጠና መስጠት
  • ልዩ ስልጠና፣ በየዩኒቨርሲቲው ያሉ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (IT) የማስተማሪያ ቴክኖሎጂዎችን በደንብ እንዲያውቁ እና ለመምህራን በቅርበት እገዛ እንዲሰጡ ተጨማሪ ስልጠና እንዳስፈላጊነቱ ለመስጠት መዘጋጀት።

ለ. ለሁለተኛ ደረጃ እና ከዚያ በታች ላሉ ት/ቤቶች

በትምህርት ሚ/ር የትምህርት መሳሪያዎች ማደራጃ መምሪያ (አሁን መኖሩን እርግጠኛ ባልሆንም) ወይም ለትምህርት መርጃ መሳሪያዎች ዝግጅት ኃላፊነት ያለበት የክልል ትምህርት መምሪያ ከትምህርት ሚ/ር የሚመለከተው ክፍል ጋር በመሆን የትምህርት መርጃዎችን (በተለይ ሳምንታዊ የክትትል ቅጽ እና ክለሳዎችን) ለሁለተኛ ደረጃ እና ከዚያ በታች ላሉ ተማሪዎች የሚያዘጋጁ የባለሞያዎች ቡድኖች በአስቸኳይ ማዋቀር እና ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረግ፣ ቡድኖቹ ሊያከናውኗቸው ከሚገቡ ተግብራት ለምሳሌ፣

  • ቡድን አንድ፣ በየክፍል ደረጃው የሚያገለግሉ የመማሪያ መፃሕፍት በበቂ ሁኔታ ተማሪዎች (በተለይም ለሁለተኛ ደረጃ) በነፍስወከፍ እንዲደርሳቸው በቂ ዝግጅት ማድረግ
  • ቡድን ሁለት፣ ከመማሪያ መፃሕፍት በተጓዳኝ ለየትምህርት ዓይነቱ ተያያዥ የሆኑ የሳምንታዊ ሂደት ክትትል ማድረጊያ ቅጽ (progress check-list) ማዘጋጀት። ይሄ የሂደት መከታተያ፣ በቴሌቪዢን እና በሬዲዮ ለሚደረግ ስርጭት መከታተያም ይጠቅማል። ለስርጭት እንዲመች የሁሉንም የትምህርት አይነቶች፣ በየክፍል ደረጃው አንድ ላይ መጠረዝ ይቻላል።
  • ቡድን ሦስት፣ እንደየትምህርት ዓይነቱ ባሕሪይ አጫጭር ክለሳዎች እና መልመጃዎችን የያዘ አንድ ጥራዝ ማዘጋጀት (ለስርጭት እንዲያመች) ሁለት እና ከዚያ በላይ የሆኑ የትምህርት ዓይነቶች አንድ ላይ ሊጠረዙ ይችላሉ።
  • ቡድን አራት፣  ከወረቀት እና የሕትመት ድርጅቶች ጋር በቅርበት መስራት እና የማስተማሪያ መርጃዎች ሕትምት ማሳለጥ
  • ቡድን አምስት፣ የማስተማሪያ መርጃዎች ስርጭትን ከየክልሉ የትምህርት ቢሮዎች ጋር በመተባበር ለተደራሾች ማሰራጨት  

Written by 

7 Replies to “ይድረስ ለሚመለከተው (ለትምህርት ሚኒስቴር)”

  1. ሠላም ደኔ፣
    የሀገራችን ትምህርት ጉዳይ እንደኢትዮጵያዊነትህ አስጨንቆህ ይህንን የመፍትሔ ሀሳብ በማቅረብህ እንደ አንድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መምህር ሳላመሰግንህ አላልፍም፡፡
    ደኔ የአቀረብካቸው አማራጥ ሀሳቦች ጥሩ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ በአተገባበሩ ወቅት ሊገጥሙ የሚችሉ ውስንነቶች (Limitation) ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ዘመን ያፈራውን ቴክኖሎጂ መጠቀም ገጠር ያለውን ተማሪ ስማርት ስልክ እንኳን የሌለውን እንዴት ልንደርሰው እንችላለን? We are applying Microsoft teams and e-learning for Post Graduate Students፡፡ አፈፃፀሙን ስገመግመው ዝቅተኛ ነው፡፡ ምክንያቱ ዋነኛ ምክንያቱ ተማሪዎቹ ለቴክኖሎጂው የሚሰጡት ትኩረት አነስተኛ በመሆኑ ትምህርቱ በሚሰጥበት ወቅት በአብዛኛው ኦንላይን ላይ አይገኙም፡፡ ሌላው የመብራነትና የኔትወርከ መቆራረጥ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ችግሮች ናቸው፡፡
    አንተ ያቀረብከው አማራጭ የማስተማሪያ መንገዶች በሚመለከተው ክፍል ትኩረት እንደሚያገኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ሊገጥሙ ከሚችሉ ተግዳሮቶችን ከመፍተሄ ሀሳቡ ጋር መወያየቱ ተገቢ ነው እላለሁ፡፡
    ፈጣሪ ሀገራችንና ህዝቧን ከመጣው ወረርሽኝ ይጠብቅ!

  2. This is a well thought advice . I hope those responsible bodies will take this cost free suggestions seriously. Good job , Denekew God bless you.

  3. ደነቀው… ግዜ ወስደህ ገንቢ የሆነ ጥቆማ መስጠትህ የሚበረታታ ነው።
    መንግስትም ሆነ የግለሰብና የጋራ የትምህርት ተቋማት፤ ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረገ የመማር ማስተማር ስርዓትን ተግባር ላይ ማዋልን ግድ የሚልበት ግዜ ላይ እንገኛለን።

    አብዛኛዎቹ ተቋማት፤ ባህላዊ ከሆነው የመማር ማስተማር ሂደት ፈቅ ማለት ባለመቻላቸው፤ የትምህርት ሂደቱ ሀገራዊ የሆነ ቀውስ ላይ ወድቋል። ቴክኖሎጂውን ተደራሽነት ባለው ሁኔታ ለተማሪዎችና ለትምህርት ተቋማቱ፤ እንዲሁም ለአስተማሪዎች ለማዳራስ ይቻል ዘንድ፤ አባሪ አድርገህ የምትጠቁማቸው፤ ነፃ (Open Source) አፕሊኬሽኖች ቢኖሩ ጥሩ ይሆናል።

    1. በትክክል አቤል። ትምህርትን ማዕከል ያደረግ የኦፕን ሶርስ (education centered open source initiative) ፕሮጀክቶች መጀመር ወደ መፍትሄዎቹ ከሚያደርሱት መንገዶች አንዱ ነው።

  4. The proposal looks perfect and belive that it is the right medicine to the problem under the current situation. If the government shows commitment, its possible to reduce all the limitations. I belive that all business and goverenment sectors could play an immense role if the goverenment organise them.
    Thank you for the initiative and contribution, credit to Mr Denekew.

Comments are closed.